… ከባለፈው የቀጠለ… የሰሙነ ሕማማት ዕለታት ስያሜ (ከኀሙስ – ቅዳሜ)

“ሐዋርያቲሁ ከበበ፥እግረ አርዳኢሁ ሐፀበ፤ኮኖሙ አበ ወእመ፤ወመሀሮሙ ጥበበ”

ኀሙስ

የሰሙነ ሕማማት ዕለተ ኀሙስ ስያሜ ጸሎተ ኀሙስ፣ የሕጽበተ እግር ቀን፣ የምሥጢር ቀን፣አረንጓዴው ኀሙስ፣ትዕዛዘ ኀሙስ፣ የሐዲስ ኪዳን ኀሙስ፥ የነጻነት ኀሙስ ይባላል።

ጸሎተ ኀሙስ ፡-

ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስን ጸሐፍት ፈሪሳውያን የአይሁድ ሊቀ ካህናት መጥተው እስኪይዙት ድረስ በጌቴ ሴማኒ በአትክልቱ ስፍራ ሌሊቱን ሲጸልይ ያደረበት ዕለት ነውና ጸሎተ ኀሙስ ይባላል። (ማቴ 26፥36)

አረንጓዴው ኀሙስ፡-

ጌታችን መድኀኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በጌቴ ሴማኒ በአረንጓዴ በተሞላ በአትክልቱ ቦታ ስለጸልየ  አረንጓዴው ኀሙስ ይባላል።

ትዕዛዘሙስ፡-

 እኔ በትኅትና ዝቅ ብዩ እግራቸውን እንዳጠብኩ እናንተም እንዲሁ አድርጉ ብሏልና ትዕዛዘ ኀሙስ ይባላል።

ሕጽበተ እግር ፡-

ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ከእኔ ተማሩ እኔ የዋህ በልቤም ትሁት ነኝና እንዳለ ትኅትናን ለማስተማር የደቀ መዛሙርቱን እግር በፍጹም ትህትና ዝቅ ብሎ ያጠበበት ዕለት በመሆኑ ሕጽበተ እግር ይባላል። ዮሐ 13፥3-14

የምሥጢር ቀን፡-

“ሲበሉም ኢየሱስ እንጀራን አንሥቶ ባረከ ቈርሶም ለደቀ መዛሙርቱ ሰጠና። እንካችሁ፥ ብሉ ይህ ሥጋዬ ነው አለ። ጽዋንም አንሥቶ አመስግኖም ሰጣቸው እንዲህም አለ። ሁላችሁ ከእርሱ ጠጡ፤ስለ ብዙዎች ለኃጢአት ይቅርታ የሚፈስ የአዲስ ኪዳን ደሜ ይህ ነው።” (ማቴ 26፥26) ምሥጢረ ቁርባንን የመሠረተበት ዕለት ነውና የምሥጢር ቀን ይባላል።

የሐዲስ ኪዳን ኀሙስ፡-

በእንስሳት ደም የሚቀርብ መሥዋዕት ቀርቶ ለዓለም ድኅነት ራሱን ያቀረበበት ቀን በመሆኑ የሐዲስ ኪዳን ኀሙስ ይባላል።ሉቃ 22፥20

የነጻነት ኀሙስ፡-

ጌታችን መድኃታችን ኢየሱስ ክርስቶስ የሰውን ልጅ ከኃጢአት ባርነት ነጻ ያደረገበት “ከእንግዲህ ወዲህ ባሮች አልላችሁም፤ ባሪያ ጌታው የሚደርገውን አያውቅምና፤ ወዳጆቼ ግን ብያችኋለሁ” (ዮሐ.15፥15) በማለት ለዲያብሎስ ባሪያ ሆኖ መኖር ማብቃቱ የተረጋገጠበት ቀን በመሆኑ የነጻነት ኀሙስ ይባላል።

ዓርብ

በሰሙነ ሕማማት ያለው ዕለተ ዓርብ የስቅለት ዓርብ፤ የድኅነት ቀን፣ መልካም ዓርብ ይባላል፡፡

የስቅለት ዓርብ፡-

ጌታችን የመድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ለአዳምና ለልጆቹ ሁሉ ቤዛ ሆኖ በመልዕልተ መስቀል ላይ ተሰቅሎ የዋለበት ዕለት ነውና የስቅለት ዓርብ ይባላል። (ማቴ 27፥35)

የድኅነት ቀን (መልካሙ ዓርብ፡-)

የስቅለት ዕለት የዕዳ ደብዳቤያችን በጌታችን በመድኃኒታችን በኢየሱስ ክርስቶስ ለመጨረሻ ጊዜ የተደመሰሰበት፤ ከአጋንንት አገዛዝ ነጻ የወጣንበት ዕለት ስለኾነ እንዲሁም ከጌታችን ስቅለት በፊት በሮማውያን ሕግ የወንጀለኛ መቅጫ ምልክት የነበረውን መስቀል ጌታችን በደሙ ቀድሶ የምሕረት፣ የዲያቢሎስ ድል መንሻ ስላደረገው፤ በሞቱ መልካሙን ሕይወት ስለሰጠን የድኅነት ቀን (መልካም ዓርብ) ይባላል፡፡ (ማቴ. 27፥1-57)

ቅዳሜ

በሰሙነ ሕማማት ያለችው ቀዳሚት ሰንበት፡- ቀዳም ሥዑር፣ ለምለም ቅዳሜ፣ ቅዱስ ቅዳሜ ትባላለች፡፡

ቀዳም ሥዑር፡-

ይኸውም የማትጾመዋ ቅዳሜ  በተለየ መልኩ የጌታችንን መከራ በማሰብ በጾም ታስባ ስለምትውል ቀዳም ሥዑር /የተሻረች ቅዳሜ/ ትባላለች ።

ቅዱስ ቅዳሜ፡-  

እግዚአብሔር አምላካችን በጥንተ ተፈጥሮ ሃያ ሁለቱን ሥነ ፍጥረታት የሚታዩትንና የማይታዩትን፣ በእግር የሚሄዱትን እና በክንፍ የሚበሩትን፣ በባሕር የሚዋኙትንና በመጨረሻም በዕለተ ዓርብ ሰውን በአርአያውና በአምሳሉ ፈጥሮ ከፈጸመ በኋላ ቅዳሜ ዕለት ከሥራው ሁሉ ያረፈበት ዕለት ናት፡፡ በዘመነ ሐዲስም የማዳን ሥራውን አከናውኖ ከፈጸመ በኋላ በቀዳሚት ዕለት በከርሰ መቃብር አድሮ በአካለ ነፍስም ሲዖልን በርብሮ ተግዘው የነበሩትን ነፍሳት ያወጣበት ዕለት በመሆኑ ቅዱስ /ልዩ/ ቅዳሜ ትባላለች፡፡

ለምለም ቅዳሜ፡-

ለምለም ቅዳሜ መባሏም ካህናቱ የምሥራች አብሣሪ የሆነውን ቄጤማ ይዘው ወደ ምእመናን ቤት በመሄድ ቀጤማ የሚያድሉበት ዕለት በመሆኑ ለምለም ቅዳሜ ትባላለች፡፡

እንበለ ደዌ ወሕማም እንበለ ፃማ ወድካም አመ ከመ ዮም ያብጽሐነ ያብጽሕክሙ ለብርሃነ ትንሣኤሁ እግዚአብሔር በፍስሐ ወበሰላም!