የሰሙነ ሕማማት (የዕለታት ስያሜ) (ከሰኞ – ረቡዕ)

“እንበለ ደዌ ወሕማም እንበለ ፃማ ወድካም አመ ከመ ዮም ያብጽሐነ ያብጽሕክሙ እግዚአብሔር በፍስሐ ወበሰላም”

ከሆሣዕና ዋዜማ ጀምሮ እስከ ትንሣኤ ያለው ሳምንት ሰሙነ ሕማማት ይባላል፡፡ እግዚአብሔር ወልድ የሰውን ልጅ ለማዳን ከእመቤታችን ከቅድስት ድንግል ማርያም ከሥጋዋ ሥጋ ከነፍሷ ነፍስ ነስቶ ተወልዶ በፈቃዱ መከራ መስቀልን እንደተቀበለ “እርሱ በእውነት ደዌያችንን ተቀበለ፤ ሕማማችንንም ተሸከመ፡፡›› (ኢሳ.53፥4‐6) በማለት ነቢዩ ኢሳይያስ የክርስቶስን ነገረ ሕማም አስቀድሞ እንደነገረን ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በፈቃዱ የተቀበለውን  መከራ መስቀል የምናስብበት ሳምንት ነው፡፡  በዚህ የዐቢይ ጾም የመጨረሻው ሳምንት(ሰሙነ ሕማማት)  ያሉ ዕለታት የየራሳቸው ስያሜ  አላቸው፡፡ እነዚህንም ስያሜዎች እንደሚከተለው እናያለን፡፡

ሰኞ፡-

  • ርግመተ በለስ (መርገመ በለስ የተፈጸመበት)

በዚህ ዕለት ጌታችን ከቢታኒያ ሲወጣ ተራበ ቅጠል ያለባትን በለስ ተመልክቶ ወደ በለሲቱ ቢቀርብ ከቅጠል በቀር ምንም ነገር አላገኘባትም ያን ጊዜ “ከአሁን ጀምሮ ለዘላለም ምንም ከአንቺ ፍሬ የሚበላ አይኑር” ማር (11፥14) በማለት ስለረገማት መርገመ በለስ የተፈጸመበት ዕለት ተብላለች።

ይኸውም “በአንጻረ በለስ ረገማ ለኃጢአት (በቅጠሏ አቅጣጫ ኃጢአትን ረገማት፤ኃጢአት ዛሬም ዘወትርም ምንም ፍሬ አይገኝብሽ ማለት ነው።)

  • አንጽሖተ ቤተ መቅደስም ይባላል

የአይሁድ ፋሲካም በቀረበ ጊዜ ጌታችን ወደ ቤተ መቅደስ ሄዶ በቤተ መቅደስ የሚሸጡትን እና የሚለውጡትን ባየ ጊዜ “ቤቴ የጸሎት ቤት ትባላለች” በማለት የሚሸጡትና የሚለዉጡትን በጅራፍ ከቤተ መቅደስ አስወጥቷቸዋል፡፡ (ዮሐ 2፡13-15)

ማክሰኞ፡-

  • የጥያቄ ቀን ይባላል

ይህ ዕለት ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በተናገረውና ባደረው፤ሰኞ ዕለት በቤተ መቅደስ ሲሸጡ እና ሲለውጡ የነበሩትን ሁሉ እየገረፈ በማባረሩ ምክንያት ለሰው ልጅ ሹመትንና ሥልጣንን የሰጠ ጌታ “በምን ሥልጣን ይህንን ታደርጋለህ?” (ማቴ 21፥ 23) ተብሎ በጸሐፍት ፈሪሳውያን ተጠይቋልና የጥያቄ ቀን ይባላል።

  • የትምህርት ቀን ይባላል፡-

ጌታችን በዚህ ዕለት በቤተ መቅደስ ረጅም ትምህርት ያስተማረበት ዕለት ስለሆነ የትምህርት ቀን ይባላል። (ሉቃ 21 ፥28)


ረቡዕ፡-

  • ምክረ አይሁድ ይባላል

ተማከሩ ኅቡረ ላዕሌየ (በኔ ላይ በአንድነት ተማከሩ) ያለው ነቢየ እግዚአብሔር ቅዱስ ዳዊት የተናገረው ትንቢት የተፈጸመበት ዕለት ነው። የካህናት አለቆችና ጸሐፍት ፈሪሳውያን ጌታችንን እንዴት መያዝ እንዳለባቸው የመከሩበትና ከአሥራ ሁለቱ ሐዋርያት አንዱ የአስቆሮቱ  ይሁዳም በሠላሳ ብር በመሳም አሳልፎ እንደሚሰጣቸው ከሊቃነ ካህናት ጋር የተነጋገረበትና እነሱም  ውሳኔ ያሳለፉበት ቀን በመሆኑ ምክረ አይሁድ ይባላል። ሉቃ 22፥1-6፤ማቴ 26፥15

  • የመልካም መዓዛ ቀን ይባላል


ጌታችን በዚህ ዕለት በስምዖን ዘለምጽ ቤት ተቀምጦ ሳለ  በመላ ዘመኗ ሕይወቷን ለዝሙት አስገዝታ ትኖር የነበረችው ማርያም እንተ ዕፍረት/ባለሽቶዋ ማርያም/ ዋጋው እጅግ ውድ የሆነ (የሦስት መቶ ዲናር ሽቱ) የአልባጥሮስ ሽቱ አምጥታ በራሱ ላይ በማር ስለቀባቸው (ማቴ 26፥6-7፤ዮሐ 12፥1-8) የመዓዛ ቀን ይባላል።

  • የዕንባ ቀን ይባላል

    ባለሽቱዋ ሴት (ማርያም እንተ ዕፍረት) ኃጢአቷን ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ይቅር እንዲላት እየለመነች በእግሩ ላይ ተደፍታ በዕንባዋ እግሩን እያጠበች በፀጉሯም እግሩን እያበሰች ስለኃጢአቷ አልቅሳለችና  ማር 14፥1 የዕንባ ቀን ይባላል።

ክርስቶስ አምላክነ ፥ ዘመጽአ ወሐመ በእንቲአነ ፥ በሕማማቲሁ ቤዘወነ፤

ንሰብሖ ፥ ወናልዕል ስሞ ኅቡረ ፥ እስመ ውእቱ ገብረ መድኃኒተ በብዝኀ(በዕበየ) ሣህሉ፡፡

…ይቀጥላል…