ካናዳ ማእከል 22ኛ ጠቅላላ ጉባኤውን በአካልና በበይነ መረብ አከናወነ፡፡
በማኅበረ ቅዱሳን የካናዳ ማእከል 22ኛ ዓመታዊ ጠቅላላ ጉባኤውን ከሐምሌ 24 እስከ 26 ቀን 2018 ዓ/ም በብሪቲሺ ኮሎምቢያ ክፍለ ሀገር በሆነችዉ በቫንኮቨር ከተማ አካሄደ። ጉባኤውን ያከናውነው በአካልና በበይነ መረብ ነው፡፡
በጠቅላላ ጉባኤውም የዋና ማእከል ተወካይ የሆኑት ሊቀ ትጉኀን ቀሲስ ዶ/ር ሙሉጌታ ስዩም በበይነ መረብ ተገኝተው የማኅበረ ቅዱሳንን መልእክት በማስተላለፍ፣ የማኅበረ ቅዱሳን የ5 መሪ ዕቅድ አጋማሽ ግምገማ በማቅረብና የጋራ ግንዛቤ በመፍጠር እንዲሁም አጠቃላይ በማእከሉ ጠቅላላ ጉባኤ በነበሩ መርሐ ግብራት ላይ በመገኘት ሐሳብ አስተያየትና አቅጣጫዎች ሰጥተዋል፡፡
ጉባኤውም ዓርብ ጸሎት በተከናወነበት ዕለት ጀምሮ የመጡት እንግዶችን ተቀብለው የጉባኤው አዘጋጆች የቫንኩቨር ንዑስ ማዕከል አባት ኅጽበተ እግር አከናውነዋል።
ቅዳሜ ሐምሌ 25 ቀን 2018ዓ.ም በጉባኤው መክፈቻ ዕለት በቫንኮቨር ኖኅተ ሰማይ ቅድስት ማርያም ወቅዱስ ሚካኤል ቤተ ክርስቲያን በሚገኙ ካህናት አባቶች ጉባኤው በጸሎተ- ወንጌል ተከፍቷል። ካህናት አባቶች በጸሎተ ወንጌል በተጨማሪ ትምህርተ ወንጌል በመስጠት፣ በአባታዊ ምክር እና ያሬዳዊ ዜማ (ወረብ) በማቅረብ ተሳትፈዋል።
በጠቅላላ ጉባኤው የማእከሉና የንዑሳን ማእከላት ዓመታዊ የአገልግሎት ክንውን ዘገባዎች ቀርበው አካሄዳቸው ተቃኝቷል፤ የቀረበው የማእከሉ የዕቅድ አፈጻጸምና የኦዲት አገልግሎት ዘገባም ውይይት ተደርጎበት ጸድቋል። እንዲሁም የወጣቶች ጉባኤ የዓመቱን የአገልግሎት ክንውን እንዲያቀርቡ ተደርጎ የተተኪ ትውልድ አገልግሎታቸውን ማጠናከር እንደሚገባ እና በሌሎች ድክመት የታየባቸውን አሠራሮች በመገምገም የመፍትሔ አቅጣጫዎች ተቀምጠዋል። በተጨማሪም ኦርቶዶክሳዊ ሕይወት ከቤተ ክርስቲያን ፈተና አንጻር በሚል ርእስ ገለጻ በማእከሉ ቀርቦ እንደ ቤተ ክርስቲያን ልጆች ምን እንደሚጠበቅብን በክርስትና እንዴት መጽናትና መትጋት እንደሚገባ የጋራ ውይይት ተካሂዷል፤ በተለያዩ ርእሰ ጉዳዮች ላይ የቡድንና አጠቃላይ ውይይት የተካሄደ ሲሆን የ2019 ዓ.ም. እቅድ ቀርቦም ውይይት ተከኗውኖ ጸድቋል። በቶሮንቶ ንዑስ ማዕከል የቀረበው የተለያዩ ተግባራት የሚከናወኑበት የማኅበሩ ማዕከላዊ ቢሮ ግዥ በተመለከተ በቀረበው ምክረ ሐሳብ ላይ ውይይት ተደርጎበታል ለተጨማሪ ማሻሻያዎችና ክትትል ወደ ማእከሉ ሥራ አስፈጻሚ ጉባኤ ተመርቷል።
በስተ መጨረሻም የአገልግሎት ግዜያቸውን በፈጸሙ የማእከሉ ሥራ አስፈጻሚዎች ምትክ ማእከሉን ለሚቀጥሉት ፫ ዓመታት የሚመሩ አዲስ ሥራ አስፈጻሚዎች ጉባኤ አባላትን በመምረጥና በማጽደቅ ጠቅላላ ጉባኤው በጸሎት ተጠናቋል ።

